ይህ ድረ ገጽ የተዘጋጀው በሕይወት አጋጣሚ በተለያዩ የዓለም ሀገራት፣ በተለይም በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ፣ ኑሯቸውን ላደረጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የአኃት አብያተ ክርስቲያናት እምነት ተከታዮች ነው። እነዚህ ምዕመናን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሌለችበትና የንስሐ አባት መያዝ አስቸጋሪ በሆነ አካባቢ የሚኖሩ ሲሆን ከእምነት ባህላቸው ወጣ ያለ ልማድ ባላቸው ሰዎች ተከበው በመኖራቸው ብቸኝነት፣ ድብርት፣ ጭንቀት እና መንፈሳዊ ዝለት ያጋጥማቸዋል። ሃሳባቸውን የሚያካፍሉት ጓደኛ፣ ዘመድ ወይም ተግባቢ ጎረቤት በቅርበት በማጣታቸው ወደ ከፋ ድብርትና ጭንቀት፣ ወደ ተለያዩ ሱሶች፣ አልፎም ራስን እስከማጥፋት ይደርሳሉ። ቤተሰብ መሥርተው የሚኖሩትም ቢሆን ግለኝነት ላይ ያተኮረ የልጆች አስተዳደግ ባለበት አካባቢ በመኖራቸውና በምዕራባውያን ባህልና ልማድ ተጽዕኖ ምክንያት በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ይገኛሉ።
ይህንን ችግር ለመፍታት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት በጠበቀ መልኩ፣ መንፈሳዊና ዓለማዊ እውቀት እንዲሁም የማማከር ልምድ ባላቸው አባቶች አማካኝነት፣ ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው በZoom፣ በWhatsApp እና በሌሎች መገናኛዎችን በመጠቀም የምክር አገልግሎት መስጠት ያስችላል። አገልግሎቶቹም፡ ኦርቶዶክሳዊ ጋብቻ፣ የልጆች አስተዳደግ፣ እጮኝነት፣ ወጣትነት፣ የሕይወት ግብ ምርጫ፣ ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች እና መንፈሳዊ አኗኗርን ጨምሮ ሌሎች በሚያጋጥማቸው ማናቸውም ችግሮች ላይ ያተኮረ ነው።
ይህ ድረ ገጽ የችግሩ ተጠቂዎች በነበሩና በቤተ ክርስቲያን አባቶች ምክር በተጠቀሙ በጎ ፈቃደኛ ምዕመናን ሃሳብ አመንጪነትና ድጋፍ የተዘጋጀ ነው። አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በነጻ የሚሰጥ እና የግለሰቦችን ሚስጥር በጠበቀ መልኩ ነው።
ይሁን እንጂ ይህ አገልግሎት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ የሆነውን፣ ከጥምቀት በኋላ የምንሠራቸውን ኃጢአቶች ለካህን ተናዘን የምንፈታበትንና ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበትን ምሥጢረ ንስሐን ለመተካት ወይም ለማስቀረት የተዘጋጀ አይደለም።
ከአባቶቻችን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ከሆኑ፣ ነጻ የምክር ቀጠሮ እዚህ ይያዙ።
በአሜሪካና በካናዳ አካባቢ የምትኖሩና በተለያዩ አጣዳፊ ችግር ውስጥ ከሆኑ፣ ተስፋ የመቁረጥ ወይም ራስዎን የመጉዳት ሃሳብ ካለዎት፣ መደበኛውን የድረ ገጽ ቀጠሮ ሳይጠብቁ በማንኛውም ሰዓት 988 ይደውሉ ወይም የጽሑፍ መልዕክት ይላኩ።